የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ራስ ገዝ የማድረግ ሂደት የሁሉንም ባለድርሻዎች ድጋፍና ትብብር እንደሚጠይቅ ተጠቆመ። በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ አስተዳደር ስትራተጂክ እቅድና ሴኔት ህግ ለማዳበር የተዘጋጀ አውደ ጥናት በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ነው።
የትምህርት ሚኒስተር ዴኤታ ክቡር አቶ ኮራ ጡሹኔ አውደ ጥናቱን ሲከፍቱ እንደገለጹትት የዩኒቨርስቲዎችን የራስ ገዝ አስተዳደር ማስፋት የመንግስት አካላት፣ የአካዳሚክ መሪዎች፣ የመምህራን፣ የተማሪዎችና የማህብረሰቡን ትብብር ይሻል። ራስ -ገዝነት የተቋማቱን ራስን በራስ የማስተዳደርና አካዳሚያዊ ነጻነትን በማረጋገጥ የት/ት ጥራት ምርምርና ፈጠራን በውጤታማነትና በብቃት ለመፈጸም እንደሚያስችል አቶ ኮራ ተናግረዋል።
አውደ ጥናቱ የመንግስት ከፍ/የት/ት ተቋማትን ራስ ገዝ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎችን ለመደገፍ የአሜሪካ መንግስት ገንዘብ ድጋፍ ማድረጉንም የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር በላይ ካሳ ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ በበኩላቸው ድጋፉ በኢትዮጵያና በአሜሪካ መንግስታት መካከል ያለው ትብብር አካል ሆኖ በከፍ/ት/ተቋማት መካከል የሚደረግ የአካዳሚክና ምርምር ልውውጥ የቆየ መሆኑን ጠቁመው ያሁኑ ድጋፍ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ዘጠኝ ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ ለመሆን የሚያደርጉትን ሂደት እንደሚያግዝ ጠቅሰዋል።
የከፍ/ት/ት የአስተዳደርና መሰረተ ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሰለሞን አብርሃ አሁን ላይ ዘጠኝ የመንግስት ከፍ/ትም/ት ተቋማት ራስ ገዝ ለመሆን የሚያስችሉ የዝግጅት ስራዎችን እያከናወኑ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
በአውደ ጥናቱ ላይ የዘጠኙም ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች፣ ም/ፕሬዚዳንቶችና የሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
ምንጭ:- ትምህርት ሚኒስቴር
