በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ የእንስሳት ህክምና ፋካልቲ ከብሩክ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ከ3ኛ እስከ 5ኛ ዓመት ለሚገኙ ተማሪዎች በእንስሳት ህክምና የላብራቶሪ ሞዴል አዘገጃጀት ክህሎትን ለማሳደግ እንዲሁም የጋማ እንስሳት ጤናን ለማስጠበቅ የሚያስችል እውቀት ላይ ያተኮረ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል።
የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ዙፋን በደዊ እንደተናገሩት "ብሩክ ኢትዮጵያ" በእንስሳት ህክምናና ደህንነት ዙሪያ በርካታ ሀገር አቀፍ ተጽዕኖ መፍጠር የቻሉ ስራዎችን እየሰራ ያለ ግብረሰናይ ድርጅት መሆኑን አስታውሰው በተለይም በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ህክምና አሰጣጥ ላይ ተጨባጭ ለውጥ ያመጡ ስልጠናዎችን፣ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ እንዲሁም የላብራቶሪ ግንባታ ስራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል።

የእንስሳት ህክምና ፋካሊቲ ዲን ዶ/ር አመነ ፈቃዱ በበኩላቸው ቀደም ሲል ለክፍሉ መምህራን የተሰጠው ተመሳሳይ ስልጠና የተሻለ ውጤት ማስገኘቱን ከግንዛቤ በማስገባት ይኸው ስልጠና ወደ ተማሪዎች መውረድ እንዳለበት ከ"ብሩክ ኢትዮጵያ" ጋር መግባባት መፈጠሩን ጠቁመው በዚህ መሰረት ከ3ኛ-5ኛ አመት ድረስ ያሉ የእንስሳት ህክምና ተማሪዎች የህክምና ሂደቱን ውጤታማና የእንስሳቱን ደህንነት በማይጎዳ መልኩ ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉበትን የእውቀትና ክህሎት ማሳደጊያ ስልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል።
ስልጠናው ባለፈው ሳምንት ለ5ኛ አመት ተማሪዎች መሰጠት መጀመሩን የገለጹት በብሩክ ኢትዮጵያ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ጤና ኦፊሰር ዶ/ር ትንሳኤ ከበደ በተለይም የጋማ እንስሳት ጤናና ደህንነት ለማስጠበቅ በክሊኒካል ላብራቶሪ ክህሎት ላይ ትኩረቱን አድርጎ እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።
