Skip to Content

ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በመንገድ ትራፊክ አደጋና ደህንነት ላይ የባለድርሻ አካላት ውይይት አካሄደ።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት በሀገርአቀፍ ደረጃ እጅግ አሳሳቢ እየሆነ በመጣው የመንገድ ትራፊክ አደጋ መከላከልና ሊወሰዱ በሚገባቸው የመንገድ ትራፊክ ደህንነት እርምጃዎች ዙርያ የባለድርሻ አካላት የምክክር ጉባኤ በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ አካሂዷል።


በውይይት መድረኩ ላይ የኢትዮጵያ አጥንት ሐኪሞች ማህበር፣ የዩኒቨርሲቲው የአጥንት ሕክምና ስፔሻሊስት ሐኪሞች፣ ከሲዳማ ክልል መንገድ ትራንስፖርትና ልማት ቢሮ፣ ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን እና ከትራፊክ ጽ/ቤት የተጋበዙ እንግዶች፣ የተለያዩ ዞኖች የመንገድ ትራንስፖርት እና ልማት ቢሮዎች፣ የሚድያ አካላት እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈውበታል።


የምር/ትብ/ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ታፈሰ ማቴዎስ መድረኩን ሲከፍቱ ባስተላለፉት መልዕክት በሀገራችን እጅግ አሳሳቢ ከሆኑ ችግሮች መካከል ቀዳሚውን ቦታ ከሚይዘው የትራፊክ አደጋና እርሱን ተከትሎ ከሚፈጠረው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንዴት ልንላቀቅ እንችላለን ብሎ መነጋገር ግዜው የሚጠይቀው አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን አስምረውበታል:: ዶ/ር ታፈሰ አክለውም የትራፊክ አደጋ ጉዳይ ተሽከርካሪን፣ አሽከርካሪን፣ የመንገድ ጥራትን፣ የትራፊክ ተቆጣጣሪዎችን እንዲሁም እግረኞችን ሁሉ የሚያሳትፍ በመሆኑ ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት እንዲቻል መሰል ተደጋጋሚ ውይይቶች በጥናት እየታገዙ መፍትሄ ለማበጀት በዩኒቨርሲቲው የማህበራዊ ኃላፊነት ዘርፍ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።



የትራፊክ አደጋ በአለምአቀፍ ደረጃ ከየትኛውም ታዋቂ ተላላፊ በሽታ በላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው ላይ ሞትና የአካል ጉዳት የሚከሰትበት እና ያላቸው የተሽከርካሪ ቁጥር እጅግ አነስተኛ ቢሆንም የችግሩን አብዛኛውን ድርሻ የሚወስዱት ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ ሀገራት መሆናቸውን ያብራሩት ደግሞ የኢትዮጵያ የአጥንት ህክምና ማህበር ፕሬዚደንትና ስፔሻሊስት ሀኪም ዶ/ር ኤፍሬም ገብረሀና ሲሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካል ተባብሮ ካልሰራበት አደጋው ብዙ አምራች ዜጎችን እንደሚያሳጣን በጥናታዊ ፅሁፋቸው አሳይተዋል::


በሀ/ዩኒ/ስፔ/ሪፈ/ሆስፒታል የአጥንት ሕክምና ስፔሻሊስት ሀኪም ዶ/ር መንግስቱ ገብረዮሐንስ በበኩላቸው የመንገድ ትራፊክ አደጋ በተለይም በሲዳማ ክልል ያለውን ገፅታ በጥናታዊ ፅሁፋቸው ለተሳታፊው ያሳዩ ሲሆን አደጋዎችን ቀድሞ ማስቀረትና መከላከል ጉዳቶችን የምንቀንስበት ዋነኛ መንገድ በመሆኑ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያሳተፈ ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዝግጅቶች አስፈላጊ መሆናቸውን ተናግረዋል።


ሌላው የውይይት መነሻ ፅሁፍ አቅራቢ በሀ/ዩኒ/ስፔ/ሪፈ/ሆስፒታል የአጥንት ሕክምና ስፔሻሊስት ሀኪም ዶ/ር ስንታየሁ ቡሳ ከአደጋ በኃላ ያለው የህክምና አገልግሎት ላይ የሚታዩትን ክፍተቶች በተለይም በባህላዊ ሕክምና ጉድለቶች ምክንያት የሚከሰቱ የሞትና የአካል ጉዳት አይነቶችን የሚገልፀውን የቦሳድ የምርምር ፕሮጀክት ሥራ አቅርበዋል::


በሲዳማ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የመንገድ ደህንነት ዳይሬክተር ዋና ኢንስፔክተር ዳንኤል ሳንኩራ በበኩላቸው በክልሉ በተለይም ከሞተር ብስክሌት ተሽከርካሪዎች ጋር ተያይዞ የሚከሰተው የትራፊክ አደጋ በቁጥሩም በአይነቱም ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ አጠቃላይ የትራፊክ ፍሰት ቁጥጥሩንና ደህንነቱን የማስጠበቅ ስራ መጠናከር እንዳለበት ተናገረዋል።


Share this post
Tags
Archive
የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ አመታዊ የምርምር አውደ ጥናት አካሄደ።