በፕሬዝዳንቱ ብርጋዴር ጀነራል ከበደ ረጋሳ የተመራው የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች ቡድን የካቲት 28/2017 ዓም በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን በሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ሊኖር ስለሚችል ትብብር ሰፊ ውይይትና የልምድ ልውውጥ አድርገዋል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ ለእንግዶቹ አቀባበል ባደረጉበት ወቅት እንደገለፁት የሀገር መከላከያ ሰራዊት በዘመናዊ እውቀትና ሳይንስ እንዲታገዝ ቁልፍ አስተዋፅኦ እያደረገ ካለው የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር መስራት ለሀገር ክብርና ሉዓላዊነት ማበርከት ነው ብለዋል።

የመከላከያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ብ/ጀኔራል ከበደ ረጋሳ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲያችን ከምስረታው አንስቶ ብዙ ጠንካራ ጎኖች ያሉት የትምህርት ተቋም ቢሆንም ባለፉት የመንግስት አስተዳደር ሥርዓቶች ብዙም ትኩረት ሳይሰጠው ቆይቶ እንደነበር አውስተው ተቋሙ ዘመኑ የሚፈልገውን አቅም እንዲኖረው ከሌሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር ለመስራት መወሰኑን ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከዚህ በፊት አጠቃላይ ተልዕኮው እየተዋጋ የሚያመርትና የሚመራ ሰው ማፍራት ላይ ያተኮረ እንደነበር የጠቆሙት ፕሬዝዳንቱ አሁን ላይ ሀገራችን የምትፈልገው አንዱ ትልቅ የሉዓላዊነቷ መሰረት በቴክኖሎጂ የበለፀገና ጠንካራ የመከላከያ ሥርዓት መዘርጋት እንደሆነ ገልፀው በተለይም ኢትዮጵያ ካለችበት ጂኦፖለቲካዊ አቀማመጥና የዓለም ተለዋዋጭ ሁኔታዎች አንፃር መንግስትና ህዝብ ልክ እንደልማት ስራው ቅድሚያ ሰጥተው ሊያጠናክሩት እንደሚገባ ታምኖበት ወደ ሥራ እንደተገባ ገልፀዋል።
የዩኒቨርሲቲያቸውን አሁናዊ አቋምና ስኬቶች ያቀረቡት የዓለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር ሻለቃ ዶ/ር በተለይ ተካ በርካታ በተግባር የተፈተሹ የወታደራዊ ምህንድስና የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎችን ያቀረቡ ሲሆን ከሌሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር መስራት የሚቻልባቸውን መስኮች አመላክተዋል።
በውይይቱ መደምደምያ ላይ የሁለቱም ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች አመራሮች ከየዘርፉ አቻዎቻቸው ጋር የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ አቅጣጫ ከሰጡ በኃላ ተቋማቱ ባላቸው የተልዕኮ ልየታ መሰረት የበለጠ ውጤታማ ትብብር እንዲኖር በተለዩ ዘርፎች ላይ በአጭር ግዜ ውስጥ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመው ወደሥራ ለመግባት ተስማምተዋል።
