በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ተማሪዎች በ "ReRed Project" በመታገዝ የስራ ፈጠራና ሙያ ማበልጸጊያ ክለብ (Entrepreneurship & Career Development Club /ECDC /) የካቲት 29/2017 ዓም መስርተዋል::
በምስረታው ላይ የተገኙት የሀ/ዩ/ም/ት/ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ታፈሰ ማቴዎስ የወ/ደ/ተ/ሀ/ኮሌጅ የአየር ንብረት ጉዳይ እንዳሁኑ አንገብጋቢ አጀንዳ ባልነበረበት የዛሬ 48 ዓመት በአርቆ እሳቢዎች ተመስርቶ ዛሬ ላይ ከሀገራችን አልፎ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፅዕኖ ፈጣሪ ምሁራንን ያፈራ መሆኑን አስታውሰው ኮሌጁ ክለቡን ለማቋቋም የሄደበትን ዝግጅትና ርቀት አድንቀዋል:: ዶ/ር ታፈሰ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ሥራ ፈጠራን ማዕከል ያደረገ አስተሳሰብ እንዲያጎለብቱ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት እንደመሆኑ ክለብ ከመመስረት ባለፈ ውጤታማ ሥራ እንዲሰራ የአስተዳደሩ ድጋፍና ክትትል መጠናከር እንደሚገባው አሳስበዋል።

ቀደም ሲል የነበረው የሀገራችን የስራ ባህል ስራ ፈጣሪዎችን የሚያበረታታ ባለመሆኑ በተለመደው የስራ ቅጥር ስርዓት ሁሉንም ምሩቅ ተጠቃሚ ማድረግ የወቅቱ ፈተና ሆኖ መምጣቱን የገለጹት የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ተሻለ ወልደአማኑኤል መሰል ክለቦችን ማቋቋም የስራ እድል ፈጠራ ተነሳሽነትን ለተማሪዎች የበለጠ ቅርብ ለማድረግ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
የተፈጥሮ ሀብትና ኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ሁለተኛ ዓመት ተማሪና የክለቡ ፕሬዚደንት የሆነው ተማሪ ተራማጅ ታመነ ክለቡ ተማሪዎች የስራ ፍላጎቶቻቸውን በመለየት ለየዘርፉ የሚያስፈልጋቸውን ክህሎት ተላብሰው ህልማቸውን መኖር የሚያስችላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስረድቷል።
