ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከኖርዌይ መንግስት ጋር ባለው የረጅም ግዜ ትብብር በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በሲዳማ ክልል ዳሌ ወረዳ በናራሞ ዴላ 01 ቀበሌ ተደራጅተው በንብ ማነብ ስራ ላይ ለተሰማሩ ሥራ አጥ ወጣቶች ማህበር 20 ዘመናዊ የንብ ቀፎዎች: የንብ መንጋ: የሥራ ማስጀመሪያ የንብ መኖና ለዘመናዊ የማር ምርት ማዘጋጃ የሚያስፈልጉ በአጠቃላይ ከአንድ ሚሊዮን ብርበላይ የሚያወጡ ሙሉ ግብዓቶችን አበርክቷል።
የዩኒቨርሲቲው የትብብር ፕሮጀክቶች ማስ/ዳይሬክተር ፕ/ር መብራቱ ሙላቱ በርክክቡ ላይ እንደገለፁት የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች ውጤታማነት የሚለካው በሚፈጥሩት የስራ ዕድል ብዛት፣ በሚፈቱትና በሚያቃልሉት የማህበረሰቡ ችግሮች፣ በዘላቂነታቸውና ፍትሐዊነታቸው በመሆኑ ለወጣቶቹ የተደረገው ሥራ ማስጀመሪያ ድጋፍ በሙያዊ ስልጠናና ተጨማሪ ድጋፍና ክትትል ዘላቂ ውጤት እንዲመዘገብ እንሰራለን ብለዋል።

የሀ/ዩ/ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ማርቆስ ፍሰሐ ዩኒቨርሲቲው በዋነኛነት በሲዳማ ክልል የሚገኙ ወጣቶችን የስራ እድል ተጠቃሚዎች በማድረግ ራሳቸውንና ማህበረሰባቸውን መጥቀም እንዲችሉ በተለያዩ ዘርፎች ሰብል ከመንግስትና መንግታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የዳሌ ወረዳ እንስሳት ሀ/ል/ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሻላሞ ሹራሞ በበኩላቸው የዩኒቨርሲቲው ድጋፍ አርሶአደርና አርብቶአደሮችን እንዲሁም የእንሰሳት ጤና ባለሙያዎችን ከማሰልጠን ባለፈ ወደ ሥራ ፈጠራ እንዲገቡ የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነቱን በሚገባ እየተወጣ እንደሚገኝ በመግለጽ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
