Skip to Content

የቀድሞ መሪዎችን ማክበርና ለአገልግሎታቸው እውቅና መስጠት ሊለመድ እንደሚገባ ተገለፀ።

በማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ አዘጋጅነት ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲን ወደ ዩኒቨርሲቲነት ካደገበት ግዜ ጀምሮ ላለፉት 25 ዓመታት እየተቀባበሉት ሲመሩ የነበሩት የቀድሞ ፕሬዚደንቶች ፕሮፌሰር ዝናቡ ገ/ማርያም፣ አምባሳደር ፕሮፌሰር አድማሱ ጸጋዬ፣ ፕሮፌሰር ዮሴፍ ማሞ እና ዶ/ር አያኖ በራሶ በአመራር ቆይታቸው የነበሯቸውን ልምዶችና ገጠመኞቻቸውን ያወጉበት ልዩ መድረክ ዛሬ በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ በድምቀት ተከናውኗል።


የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚደንትና የፕሬዝዳንቱ ተወካይ ዶ/ር ኢ/ር ፍሰሐ ጌታቸው መድረኩን ሲከፍቱ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አንጋፋ ከሚባሉት የሀገሪቱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል አንዱ ለመሆን የበቃው በአጠቃላይ የለውጥ ጉዞው ውስጥ የቀድሞ ፕሬዚደንቶች የአመራር ጥበብና ለዩኒቨርሲቲው ሁለንተናዊ እድገት የነበራቸው መሰጠት መሆኑን ጠቅሰው ይህ መድረክ መዘጋጀቱ የአሁኑና መጪው ጊዜ አመራሮችን የሚያበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።



የማ/ሳ/ስነ-ሰብ ኮሌጅ ዲንና የፕሮግራሙ አስተባባሪ ፕሮፌሰር ዘለቀ አርፍጮ በበኩላቸው መሪነት ከፍተኛ ስብእናን የሚጠይቅና በቅብብሎሽ የሚሰራ ኃላፊነት እንደመሆኑ የቀድሞ አመራሮችን ማክበርና ላበረከቱት አስተዋፅኦ እውቅና መስጠት ለተቋማዊ እድገት ቀጣይነት በማማከርና ልምዳቸውን እያካፈሉ ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ ለቀጣይ መሪዎች ትብብራቸውን እንዲቀጥሉ ማመቻቸት ሊለመድ የሚገባው ባህል መሆኑን ተናግረዋል።



በት/ሚኒስቴር የምርምር ዴስክ ኃላፊና የዕለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር አቡኑ አረጋ በሰጡት አስተያየት ታላላቆችንና የቀድሞ አመራሮችን ማመስገን ብሎም አስፈላጊውን እውቅና መስጠት ተቋማዊ ባህል ሆኖ መቀጠል የሚገባው ልምድ መሆኑን እንደተረዱ ገልጸው በዚህ መልኩ የሚካሄደው ቅብብሎሽ ዩኒቨርሲቲውን በዘላቂነት እያሻሻሉ ለማስቀጠል ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።


በዶ/ር መልሰው ደጀኔ ጠያቂነት በተካሄደው 'የቀድሞ ፕሬዚደንቶች ወግ' ላይ ዩኒቨርሲቲውን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት ሲረከቡ ምን እንደተሰማቸው፣ መሪነት ለነሱ ምን ማለት እንደሆነ፣ በኃላፊነት ዘመናቸው የተገበሩት የአመራርነት ፍልስፍና ምን እንደነበር፣ የሚቆጫቸው ውሳኔ ወይም ገጠመኝ ከነበረ፣ በፕሬዚዳንትነት ቆይታቸው ያከናወኗቸው የለውጥ ስራዎች እንዲሁም የገጠሟቸውን ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች እንዴት እንደተወጡ በምልሰት በማንሳት ልምዶቻቸውን ያካፈሉ ሲሆን በመጨረሻም የእውቅናና ምስጋና ስጦታ ተበርክቶላቸዋል።

Share this post
Tags
Archive
በንብ ማነብ ሥራ ላይ ለተሰማሩ ወጣቶች ድጋፍ ተደረገ