የበንሳ ዳዬ ካምፓስ አመታዊ የምርምር አውደ ጥናት አካሄደ
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የበንሳ ዳዬ ካምፓስ በ2016 ዓ.ም ተጀምረው የተጠናቀቁ አምስት የዲሲፕሊነሪ ምርምሮች የገመገመበት ዓመታዊ መድረክ አካሂዷል::
የሀ/ዩ የምርምር ፕሮግራም አስተባባሪ ዶ/ር ንጉሴ አፈሻ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለጹት ሀዋሳ እንደ ምርምር ዩኒቨርሲቲነቱ ወቅታዊና ችግር ፈቺ ምርምሮችን የማካሄድ ኃላፊነት ስላለበት ሁሉም ኮሌጆች በየወቅቱ የሚሰሯቸውን ምርምሮችን በቁጥርና በጥራት ማላቅ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። ዶ/ር ንጉሴ መንግስት የምርምር ዩኒቨርሲቲዎችን ለመደገፍ ለምርምር የሚመደበውን በጀት ከዓመታዊው በጀታቸው ከ2% ወደ 5% እንዲያድግ ማድረጉን ተከትሎ ከመጪው አመት ጀምሮ ጭብጥ ተኮር ምርምሮች የበለጠ ትኩረት እንደሚሰጣቸውም አክለዋል።

የዳዬ ካምፓስ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ፍሬው ካሳ በበኩላቸው ካምፓሱ በቁጥር ዝቅተኛ የምርምር ስራዎችን ከሚያከናውኑ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጆች አንዱ እንደነበረ አስታውሰው በም/ት/ም/ፕሬዚደንት ጽ/ቤት በኩል በተደረገለት ከፍተኛ ድጋፍ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል። የተሰሩ ምርምሮችን በጥልቀት በባለሙያዎች መገምገም የተገኘባቸውን ክፍተቶች በመለየት የተሻለ ሥራ ለመስራትና ወደ ተግባር ለማስገባት ስለሚያግዝ አውደጥናቶቹ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ዶ/"ር ፍሬው ገልጸዋል።
የበንሳ ዳዬ ካምፓስ ምርምርና ትብብር ተ/ዲን አቶ ማቴዎስ በዕለቱ ከካምፓሱ ተመራማሪዎች የተሰሩት አምስት የምርምር ጽሁፎች ቀርበው ሳይንሳዊ መንገድ ተከትለው ስለመሰራታቸው: ምን ያህል በተግባር ችግር ፈቺ ሊሆኑ እንደሚችሉ ከተሳታፊዎች ጥያቄዎችና አስተያየቶች በመቅረባቸው ለሌሎች ተመራማሪዎችም ልምድ የሚቀስሙበት መድረክ መሆኑን ተናግረዋል።
