ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ለሲዳማ ዲዛይንና ግንባታ ቁጥጥር ኢንተርፕራይዝ ያለማውን የERP ሶፍትዌር ሲስተም ለመሸጥ ተፈራረመ::
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ከሲዳማ ዲዛይንና ግንባታ ቁጥጥር ኢንተርፕራይዝ ጋር በዩኒቨርሲቲው የአይ ሲ ቲ ባለሙያዎች የበለፀገውን ERP ሶፍትዌር ሲስተም ልማትና ትግበራ እንዲሁም የእውቀት ሽግግር ለማድረግ የሚረዳውን ስምምነት ታህሳስ 24/2017 ዓም ተፈራርሟል::
የሀ/ዩ ምርምርና ትብብር /ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ታፈሰ ማቴዎስ ዩኒቨርሲቲው ከኢትዮጵያ አልፎ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ እየሰሩ ያሉ የሶፍትዌር ባለሙያዎች እንዳሉት ገልጸው የሲዳማ ክልል ዲዛይንና ግንባታ ቁጥጥር ኢንተርፕራይዝ ሲስተም አውቶሜት ለማድረግ በጠየቀው መሰረት የሚሰራው ስራ ደረጃውን ጠብቆ እንዲካሄድ ክትትልና ድጋፍ ተጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው ተናግረዋል። ዶ/ር ታፈሰ ዩኒቨርሲቲው በሶፍትዌር ልማት ስራው የሀገራችንን ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ዕቅድ እውን ለማድረግ ሰፋፊ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን አውስተው ኢንተርፕራይዙ ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር ለመስራት በመምጣቱ አመስግነዋል::
የሲዳማ ክልል ዲዛይንና ቁጥጥር ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢ/ር ይርጉ ታደሰ በስምምነቱ ወቅት እንዳሉት ኢንተርፕራይዙ ሁሉንም ሥራዎች ዲጅታይዝ ለማድረግና ለደንበኞቹ የተቀላጠፈና በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት ሰጥቶ ትርፋማ ለመሆን ሶፍትዌሩ እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል:: ኢንተርፕራይዙ እንደ ተቋም የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት፣ የደንበኞችን ፍላጎት ለሟሟላትም ሆነ ትርፍ ለማመንጨት ዲጂታላይዜሽን ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ሆኖ መገኘቱንም አክለዋል።
የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ አሳየኸኝ ግርማ እንደገለፁት በተደረሰው የውል ስምምነት መሰረት የሰው ሀብት መረጃ አያያዝ ሲስተም/ Human Resource Management System ፣ የንብረት አስተዳደር ሲስተም/ Property Management System፣ የፕሮጀክትና ኮንትራት አስተዳደር ሲስተም/ Project and Contract Administration Management System፣ የፋይናንስ አስተዳደር ሲስተም/ Finance Management System፣ የሰነድ አያያዝ ሲስተም/ Document Management System እና የደንበኛ መረጃ አስተዳደር ሲስተም/ Customer information management system በአንድ ላይ የተቀናጀ ሶፍትዌር ሲስተም/ Enterprise Resource Planning Software/ የማልማትና እና ሲስተሞቹን ለመጠቀም ከሚያስችል የዕውቀት ሽግግር የማከናወን ስራን በመስጠት ሁሉንም የስራ ዘርፎች ውጤታማ የማድረግ ስራ ይሰራል ብለዋል።