የፊቼ ጫምባላላ በዓል ዋዜማ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ በድምቀት ተከበረ።
በዩኔስኮ ዓለም አቀፍ የማይዳሰስ ሀብት ሆኖ የተመዘገበው የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ ፊቼ ጫምባላላ በዓል በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ አፍሪካ ህብረት አዳራሽ በድምቀት ተከበሯል።
በሲዳማ ጥናት ተቋም የተዘጋጀው በሀገር ሽማግሌዎች ምርቃት የተጀመረውና በሙዚቃ: ድራማና ቄጣላ የታጀበው ፕሮግራም የሲዳማ ዘመን አቆጣጠር ላይ በጥናታዊ ፅሁፍ የተደገፈ ገለፃ የተደረገበት እንዲሁም ከሁሉም ኮሌጆች የቀረበውና የፍቅርና የአንድነት መገለጫ በሆነው የሲዳማ ባህላዊ ምግብ "በሻፌታ" ደምቆ የተከበረው አመታዊ የፊቼ ጫምባላላ ሲምፖዚየም ላይ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችና ጠቅላላው ማህበረሰብ ተሳትፈዋል::

የሀ/ዩ ፕሬዚደንት ዶ/ር ችሮታው አየለ እንደተናገሩት ሁሉም ህዝቦች የየራሳቸው የሆነ ባህልና እሴት እንደሚኖራቸው ይህንንም አስደማሚ ባህል በጋራ በማክበር የባህል ትስስር ማጠናከር እንደሚገባ አስታውሰው በአለምአቀፍ ደረጃ እውቅና ያገኘውንና ልዩ የሲዳማ ህዝብ መገለጫ የሆነውን የፊቼ ጫምባላላ በዓል በጋራ ለማክበር እንኳን አደረሰን ብለዋል። ፕሬዝዳንቱ አክለውም ይሄንን በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ ድንቅ ባህላዊ እሴት ለቀጣይ ትውልድ ሰንዶ በሳይንሳዊ ጥናቶች ደግፎ ለማስተላለፍ የሚሰሩ ሥራዎች ላይ ዩኒቨርሲቲው ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል::
የሀ/ዩ የሲዳማ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ዶ/ር ስዩም ዩንኩራ የሲዳማ ህዝብ የዘመን መለወጫ ፊቼ ጫምባላላ በዓል በUNESCO ከተመዘገበ አስረኛ አመቱን ማስቆጠሩን አስታውሰው በእነዚህ አመታት ውስጥ የበዓሉን እሴቶች በስፋት ተደራሽ የማድረግ፣ ባህላዊ ይዘቱን ሳይለቅ እንዲከበርና የሰላም ተምሳሌትነቱን የሚያጎሉ ስራዎች በተቋሙ አማካኝነት መሰራቱን ገልጸዋል።
