Skip to Content

የኢትዮጵያ ምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተመሠረተ።

ትዮጵያ ምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተመሠረተ።


በኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስቴር እውቅና ያለው የኢትዮጵያ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም (Ethiopian Research Universities Forum) ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ስምንቱ የኢትዮጵያ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች እና ሁለቱ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎችን ይዞ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አፄ ቴዎድሮስ ስታዲየም በተዘጋጀው ስነስርዓት ላይ ዛሬ በይፋ ተመስርቷል።


ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲን ወክለው ፕሬዚዳንቱ ዶ/ር ችሮታው አየለ በምስረታ ስነስርዓቱ ላይ የተገኙ ሲሆን በመድረኩ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ፕሬዚዳንቶችና ተወካዮች፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ምሩቃን፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።


የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን የፎረሙ ሰብሳቢ ሆነው የተመረጡ ሲሆን፣ በመክፈቻ ንግግራቸውም የፎረሙን ዓላማ እና አስፈላጊነት በዝርዝር አብራርተዋል። ዶ/ር አስራት የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ችግር ፈቺ ምርምሮችን በማከናወን፣ የማህበረሰብ አገልግሎት በመስጠት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርገው መስራት እንዳለባቸው አበክረው ገልጸዋል።


ፎረሙ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች በብሔራዊ ልማት፣ ፈጠራ እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት መድረክ የሚተባበሩበት እና በጋራ የሚሠሩበት የትስስር መድረክ ሆኖ እንደሚያገለግል ተገልፅዋል።


የፎረሙ አባል ዩኒቨርሲቲዎች በዋናነት በምርምር፣ በድኅረ ምረቃ ፕሮግራሞች፣ በመምህራን ልማት እና በፈጠራ ማዕቀፎች ላይ በትብብር እንደሚሠሩ እንዲሁም ለብሔራዊ ፖሊሲዎች ግብዓት ማቅረብ፣ የትብብር ማዕቀፎችን ማጠናከር እና ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖን ማሳደግ የፎረሙ ተቀዳሚ አላማዎች እንደሚሆኑ ታውቋል።

Share this post
Tags
Archive
የፊቼ ጫምባላላ በዓል ዋዜማ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ በድምቀት ተከበረ።