በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ "የተቀናጀ የጤና ሴክተር ትራንስፎርሜሽን፣ ፈጠራ እና ትምህርት (H-STILL)" በሚል ርዕስ በወንዶ ገነት ወረዳ ሞዴል የጤና ሥርዓትን ለመፍጠር የተቀረፀ የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮጀክት የማስጀመሪያ ውይይት ከሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ጥር 6/2018 ዓ/ም ተካሂዷል።
የህ/ጤ/ሳ/ኮ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ፍጹም ወ/ገብርኤል ለውይይቱ ተሳታፊዎች ባስተላለፉት መልዕክት ኮሌጁ በ ሪፈራል ሆስፒታል በኩል ለህብረተሰቡ ከሚሰጠው መጠነ ሰፊ የጤና አገልግሎት ባሻገር የጤና ባለሙያዎችን በማሰልጠን፣ ችግር ፈቺ ምርምሮችን በማካሄድ እና በክልሉ የሚገኙ የጤና ተቋማትን በቁሳቁስ እንዲሁም ባለሙዎችን በማማከር (mentoring) በመደገፍ በርካታ ተጨባጭ ለውጥ ቢያስመዘግብም የአሁኑን ዓይነት ልዩ የማህበረሰብ አገልግሎት በመስጠት ላይ ውስንነት እንደነበረ ገልጸዋል። ዶ/ር ፍፁም ይሄንን ፕሮጀክት የቀረፁ የኮሌጁን ተመራማሪዎች እና በጀት መድቦ እንዲሰራበት ያፀደቀውን የዩኒቨርሲቲውን የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት አመስግነው ለተግባራዊነቱ የክልሉን ጤና ቢሮ ትብብር ጠይቀዋል።

የሲዳማ ብ/ክ/መንግስት የጤና ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ በላይነህ በቀለ በመክፈቻ ንግግራቸው ሞዴል የጤና ወረዳዎችን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመፍጠር የተጀመረውን አሰራር ለማሳካት በ5 መመዘኛዎች መሰረት ቀደም ሲል በሞዴልነት ተይዘው የነበሩ ወረዳዎችን እንደገና የመገምገም ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው የወንዶገነት ወረዳን በጤና አገልግሎት ሞዴል አድርጎ ማቅረብ በሚቻልበት ፕሮጀክት ዙሪያ በይበልጥ ተቀራርቦ ለመስራት የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን ተናግረዋል።
ሁሉም የዩኒቨርሲቲው ኮሌጆች ከመማር ማስተማር እና ምርምር ስራዎቻቸው በተጨማሪ በማህበረሰብ ጉድኝት ስራ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በየጊዜው የሚሰሩት ስራ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን የገለጹት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ማርቆስ ፍሰሐ የህ/ጤ/ሳ/ኮ በዚህ ረገድ በጤናው ዘርፍ እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል ብለዋል። አቶ ማርቆስ በመንግስት ፖሊሲ ዩኒቨርሲቲዎች የማህበረሰብ አገልግሎት ሳይሆን በዋናነት ህብረተሰቡን እና አጋር ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የማህበረሰብ ጉድኝት ላይ እንዲሰሩ መሆኑን ጠቅሰው የአሁኑ ፕሮጀክት ይሄንን መርህ ወደ ተግባር የሚቀይር መሆኑን ገልፀዋል::
የኮሌጁ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር እና የፕሮጀክቱ አባል የሆኑት ዶ/ር ረቂቁ ፍቅሬ በበኩላቸው የማህበረሰቡን የጤና አገልግሎት የማግኘት መብት በተሻለ ሁኔታ ለመፈጸም ለሌሎች እንደ መነሻ የሚሆን ሞዴል ወረዳ ተግባራዊ የማድረግ ስራ ይሰራል ያሉ ሲሆን የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር ቀነኒ ጉተማ ስለፕሮጀክቱ አጠቃላይ ሂደት ማብራሪያ በመስጠት ከፕሮጀክቱ መተግበር በኋላ በሚጠበቀው ውጤት ዙሪያ ገለጻ አቅርበዋል።
