በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስና ስነሰብ ኮሌጅ ባለፈው በጀት ዓመት በነበረው የእቅድ አፈፃፀም ውድድር በሁለት ተከፍለው ከተወዳደሩት ኮሌጆች መካከል በአንደኝነት ማጠናቀቁን አስመልከቶ የኮሌጁን አጠቃላይ የአካዳሚክ እና አስተዳደር ሰራተኞች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ልዩ የአብሮነት እና በጎ አድራጎት መርሃግብር ጥር 9/2018 አካሂዷል።
ከዋናው ግቢ ወደ ሐዋሳ ሀይቅ በመሄድ በጋራ የጀልባ ሽርሽር በማድረግ የተጀመረው ፕሮግራም በሐዋሳ ሜሪ ጆይ አረጋውያን መርጃ ማዕከል በተካሄደ የአብሮነት ምሣ እና የደም ልገሣ ፕሮግራም ተጠቃሏል።
የኮሌጁ ዲን ፕሮፌሰር ዘለቀ አርፊጮ ኮሌጁ ይሄንን የአንደኛነት ደረጃ ያገኘው እያንዳንዱ የክፍሉን ሥራ በኃላፊነትና በትጋት ስለተወጣ በመሆኑ ስኬቱ የሁሉም የኮሌጁ ማህበረሰብ እና አጋር አካላት ነው ብለዋል:: ዲኑ በኮሌጁ አጠቃላይ መምህራን በጎ ፈቃደኝነት ከአምና ጀምሮ በየወሩ 100 ብር ከደመወዛቸው እያዋጡ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ለመድረስ እያደረጉት ላለው ዘላቂ አስተዋፅኦ አመስግነው ይህን ዕድል በሰፊው ለመጠቀም የሶስዮሎጂ ት/ክፍል ከሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ እና የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን ት/ክፍል ከግሎባል ፒስ ባንክ ጋር የትብብር ስምምነት በመፈራረም እየሰሩ መሆኑን ገልፀው ኮሌጁ በዚህ ረገድ ተጨማሪ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ከተማሪዎቹ ጭምር በንቃት በማሳተፍ እንደሚሰራ ቃል ገብተዋል።

የሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ሲ/ር ዘቢደር ዘውዴ በበኩላቸው የሀ/ዩ/ማ/ሳ/ስ/ሰ/ኮሌጅ ይህንን ቅዱስ ተግባር በመፈፀሙ ከልብ አመስግነው ባለፈው ዘመናቸው መልካም ሕይወት፣ ልጆች፣ እውቀት፣ ሥራ እና ጤና የነበራቸውና በአቅመ-ደካማነት ዘመናቸው ግን ደጋፊ ያጡ አረጋውያንን 'አለንላችሁ' ማለት እጅግ ልብን የሚያስደስት፣ በፈጣሪ ፊትም የሚያስመሰግን፣ ተግባር እንደመሆኑ ይሄ አሰራር በሌሎችም ዘንድ በሰፊው ሊለመድ ይገባል ብለዋል:: ሲ/ር ዘቢደር ድርጅታቸው በቅርቡ በሐዋሳ ከተማ ያስጀመረውን የኩላሊት እጥበት ማዕከል በአባልነት እንዲቀላቀሉ፣ ከጎዳና ላይ የተነሱ ሕፃናትን ፊደል በማስቆጠር ወደ ትምህርት ቤት ለማስገባት በሚሰራው ሥራ ላይ እንዲሳተፉ፣ የወጣቶች ማዕከሉን በእውቀትና በምርምር እንዲደግፉ፣ በየቤቱ የሚረዱ አረጋውያንን በትንሽ አስተዋፅኦ እንዲረዱ፣ እንደ ሽምግልና እና ሰርግ ያሉ የተለያዩ ማህበራዊ ፕሮግራሞችን ከአረጋውያኑ ጋር በማከናወን የምርቃት በረከት እንዲያገኙ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በዚሁ ፕሮግራም ላይ የተገኙት የግሎባል ፒስ ባንክ እና አቤነዘር የሕፃናት መርጃ መስራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ አርጋው አየለ እና የሻሎም ቢዝነስ ኮሌጅ ባለቤት ዶ/ር ፀጋዬ ማቲዎስ እንዲሁም የሐሮኒ ሆቴል ባለቤት ወ/ሮ ሙሉ ጠንክር ለማዕከሉ የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን የኮሌጁ ሰራተኞችም የዲያልሲስ ማዕከል አባልነት ምዝገባ: የገንዘብ አስተዋፅኦ እና የደም ልገሣ አድርገው በአረጋውያን ተመርቀዋል።
