Skip to Content

የወባ በሽታ ስርጭት አሁናዊ ሁኔታን የሚዳስስ ሴሚናር ተካሄደ

የወባ በሽታ ስርጭት አሁናዊ ሁኔታን የሚዳስስ ሴሚናር ተካሄደ።


በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት እንደ አዲስ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየጨመረ በመጣው የወባ በሽታ ስርጭት እና ዩኒቨርሲቲው በዚህ ዙርያ እያከናወነ ስላላቸው ሥራዎች እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው ቀጣይ ሚና ላይ ለመመካከር ያለመ ሴሚናር አዘጋጅቷል::


ታህሳስ 24/2017 ዓም በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ በተካሄደው ሴሚናር ላይ ከአሜሪካው ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የተጋበዙት የዘርፉ ከፍተኛ ተመራማሪ ሳይንቲስት ዶ/ር ሰለሞን ክብረት እና ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ህ/ጤ/ሣ/ኮ ተመራማሪው ዶ/ር ዳዊት ሐዋርያ ለውይይት መነሻ የሚሆን ፅሁፍ ያቀረቡ ሲሆን በመድረኩ ላይ ከተለያዩ ክልሎች የተወከሉ የዘርፉ ባለሙያዎችና የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ተመራማሪዎችና ሚድያዎች ተሳትፈዋል።


ዶ/ር ሰለሞን ክብረት የወባ በሽታ በዓለም ላይ በገዳይነታቸው ከሚጠቀሱት መካከል ግንባር ቀደም ድርሻ እንዳለው ጠቅሰው በተለይ በአፍሪካ አህጉር ከባድ የማህበረሰብ ጤና እክልና የኢኮኖሚ ተግዳሮት እንደሆነ ገልፀዋል:: በሽታው ባለፉት ዓመታት በቅንጅት በተሰሩ በርካታ ስራዎች የተሻለ ቁጥጥርና የመከላከል አቅም ተገንብቶ እንደነበር ያነሱት ዶ/ር ሰለሞን ይሁን እንጂ ከጥቂት አመታት ወዲህ የወባ በሽታ ስርጭት ዳግም ማገርሸቱን፣ በሀገራችን አዲስ የወባ አስተላላፊ ትንኝ ዝርያ መገኘቱን፣ በየአካባቢው የሚከሰቱ ግጭቶች መበራከት፣ በህብረተሰቡና በጤና ተቋማት የተፈጠሩ ዝንጉነቶች እንዲሁም በኮቪድ ምክንያት የተፈጠረው የጤናው ሥርዓት መዳከም ዋነኞቹ ባለድርሻዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል::


የወባ በሽታ ዳግም ስጋት ወደማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ በአዳዲስ ምርምሮች የተደገፈ ስትራቴጂካዊ እቅድ ተዘጋጅቶ መተግበር እንደሚገባውም ዶ/ር ሰለሞን አሳስበዋል።


ዶ/ር ዳዊት ሐዋሪያ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በቅርቡ ባካሄደው ጥናት በሲዳማና አጎራባች ክልሎች ያለው የወባ በሽታ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ጠቅሰው በአንጻሩ የአጠቃላይ ማህበረሰቡ ግንዛቤ እምብዛም ለውጥ እንዳላሳየ ተናግረዋል። የውይይት መድረኩ ዋነኛ አላማ ለወባ በሽታ ስርጭት አጋላጭ የሆኑ ምክንያቶችን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመለየት ውጤቶቹን ቀምሮ መፍትሔ ለማስቀመጥ መሆኑን በመጠቆም ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ እንደ ምርምር ዩኒቨርሲቲነቱ የሚጠበቅበትን ድርሻ ለመወጣት አዲስ የምርምር ማዕከል በማቋቋም እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።


የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር ችሮታው አየለ በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ እንደተናገሩት ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሚገኝበት አካባቢ የወባ አምጪ ትንኞች ለመራባት አመቺ በሆነው የስምጥ ሸለቆ አካባቢ እንደመሆኑ እንደ አዲስ ያገረሸውን ወረርሽኝ ለመቆጣጠርና አዳዲስ የመከላከያ መንገዶችን ለማስተዋወቅ የሚረዳውን የወባ ምርምር ማዕከል አቋቁሞ ሥራ መጀመሩ አንድ ነገር ሆኖ ማዕከሉን ወደ ልህቀት ማዕከል ለማሳደግ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቁርጠኛ መሆኑን ገልፀዋል::


የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታፈሰ ማቲዎስ እንዲሁ የማዕከሉ መጠናከር ላይ ሁሉንም ባለድርሻ አስተባብሮ ሳይንሳዊ የሆነ መፍትሄ ማመንጫ ማዕከል ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ ቃል ገብተዋል::


Share this post
Tags
Archive
ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ለሲዳማ ዲዛይንና ግንባታ ቁጥጥር ኢንተርፕራይዝ ያለማውን ሶፍትዌር ሲስተም ለመሸጥ ተፈራረመ