Skip to Content

4ኛው ሀገር አቀፍ የምርምር ኮንፈረንስ ተካሄደ

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የህግና ገቨርናንስ ኮሌጅ "የኢትዮጵያ የመሬት ሪፎርም: የንብረት ይዞታ ደህንነትን፣ የመሬት አስተዳደር፣ እድገት፣ ከተሜነትን ማስፋፋትና ማስቀጠል" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ ሀገር አቀፍ የምርምር ኮንፈረንስ የካቲት 20/2017 ዓም በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ተካሂዷል።


የምርምር ፕሮግራሞች ዳይሬክተር ዶ/ር ራሕመቶ አበበ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለፁት መሰል ሀገር አቀፍ ኮንፈረንሶች የምርምር ስራዎችን ውጤቶች ለሌሎች የዘርፉ ምሁራንና ባለድርሻ አካላት በማጋራት የእውቀት ሽግግርን ያሳልጣሉ ብለዋል። አክለውም የህግና ገቨርናንስ ኮሌጅ በሀገራችን የሚገኙ አከራካሪ ህጎችን ከአለምአቀፋዊ ልኬቶች አንጻር በምርምር የተደገፈ ዳሰሳ በማድረግ እንዲለወጡና እንዲሻሻሉ የማድረግ አስተዋጽኦውን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ገልጸዋል።



የህግና ገቨርናንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ደብረወርቅ ደበበ በዚህ ዓመት ለሁለተኛ ጊዜ ባዘጋጁት ሀገርአቀፍ የምርምር ኮንፈረንስ ላይ በሀገራችን በተለይም በመሬት አስተዳደር ህጎች: አዋጆችና የሪፎርም ሥራዎች ላይ ያነጣጠሩ የምርምር ጽሁፎች ቀርበው ምሁራዊ ክርክርና ገንቢ ሃሳቦች እንዲፈልቁና ለፖሊሲና ህግ አውጭ አካላት ጠቃሚ ግብዓቶች እንደሚኖሩ ይጠበቃል ብለዋል።


በኮንፈረንሱ ላይ ቁልፍ ንግግር ያቀረቡት የወ/ደ/ተ/ሀ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ተሻለ ወ/አማኑኤል በበኩላቸው መሬት በሀገራችን ስርአተ መንግስታት ውስጥ ከፍተኛ ጥያቄዎችና ክርክሮች የሚነሱበት ሀብት እንደመሆኑ "በኢትዮጵያ ያለው የመሬት አስተዳደርና ፖሊሲ በሀገሪቱ ለተከሰቱ ግጭቶችና የከረረ ብሔርተኝነት የነበረው አስተዋጽኦ"፣ "የፌደራሊዝም ስርዓትና የመሬት አስተዳደር ቁርኝት" 

"የገጠር መሬት አስተዳደርና የመንግስት የመሬት ባለቤትነት" በሚሉ አርዕስቶች ላይ ሰፋ ያሉ ሃሳቦችና የውይይት መነሻ ጥያቄዎችን አቅርበዋል።


በመድረኩ የተሳተፉ የሲዳማ ክልል የመሬት አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊዎች በምርምሩ የተነሱ አዳዲስ የመሬት አያያዝና አስተዳደር ጽንሰ ሀሳቦች በአሁኑ ወቅት በተግባር ላይ ካሉት ህጎችና አዋጆች ጋር የማስተያየትና የማካተት ስራዎች በቀጣይ በመንግሥት ደረጃ እንደሚሰራባቸው ጠቁመዋል።

Share this post
Tags
Archive
በእንስሳት ህክምና የክሊኒካል ላብራቶሪ ክህሎት ስልጠና እየተሰጠ ነው