በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ የስታቲስቲክስ ት/ክፍል ለዩኒቨርሲቲው የድህረ ምረቃ ተማሪዎች በምርምር ስራዎች ላይ አጋዥ የሆኑትን የ"SPSS-R" እና "STATA" ሶፍትዌሮች አጠቃቀም ላይ የሁለት ቀናት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ከየካቲት 27-28/2017 ዓም እየሰጠ ነው።
ሶፍትዌሮች በምርምር ስራ ላይ ከመረጃ አሰባሰብ እስከ የመጨረሻው ውጤት ትንታኔ ድረስ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ የገለጹት የተ/ቀ/ሳ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ዙፋን በደዊ ተመራማሪዎች እነዚህን ሶፍትዌሮች ጠንቅቀው ማወቅና መጠቀም እንዲችሉ ተደጋጋሚ ስልጠናዎች ያስፈልጋሉ ብለዋል። ዶ/ር ዙፋን የስታቲስቲክስ ትምህርት ክፍል መምህራን በራሳቸው ተነሳሽነት በየዓመቱ ተመሳሳይ ስልጠና በመስጠት አዎንታዊ ድርሻ እየተወጡ እንደሆነ ገልፀው ምስጋናቸውን በኮሌጁ ስም አቅርበዋል።

የስታቲስቲክስ ት/ክፍል ኃላፊ መምህርት ውብእጅግ እንየው በበኩላቸው ስልጠናው በዩኒቨርሲቲው ስር ለሚገኙ የሁሉም ኮሌጆች የማስተርስና ዶክትሬት መርሃግብር ተማሪዎች የተዘጋጀና በት/ክፍሉ አንጋፋ መምህራን እየተሰጠ እንደሆነ ገልፀው ሶፍትዌሮቹ መረጃን በማጥራት፣ ኮድ በማድረግ፣ በመተንተን እንዲሁም ውጤት በማስቀመጥ የምርምር ስራዎችን የምያቀሉ በመሆናቸው ሰልጣኝ ተመራማሪዎች ትኩረት ሰጥተው ስልጠናውን በመከታተል ተጠቃሚነታቸውን እንደሚያረጋግጡ እምነት አለኝ ብለዋል።
