በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የበንሳ ዳዬ ካምፓስ ከዩኒቨርሲቲው የሙያ ማበልጸጊያ ማዕከል ጋር በመተባበር ለተመራቂ ተማሪዎች የስራ ፈጠራ ክህሎት እና የመቀጠር ዝግጁነት ላይ ስልጠናተሰጥቷል::
የበንሳ ዳዬ ካምፓስ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ፍሬው ካሳ ባስተላለፉት መልዕክት በየሙያ ዘርፉ ሳይንሳዊ እውቀት ገብይተው ከዩኒቨርሲቲ የሚወጡ ምሩቃን እውቀታቸውን በመጠቀም ራሳቸውንም ሆነ ሀገራቸውን የሚጠቅሙበትን ስርዓት ለማመቻቸት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል። አዳዲስ ተመራቂ ተማሪዎች ገበያው የሚፈልገውን ልምድና ክህሎት በቀላሉ ለማግኘት እንደሚቸገሩ የገለጹት ዶ/ር ፍሬው ይህንን ታሳቢ በማድረግ መሰል የስራ ፈጠራና የስራ ዝግጁነት ክህሎት ማጠናከርያ ስልጠናዎች ለተማሪዎች መስጠት ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ ገልፀዋል።

ስልጠናውን ያስተባበሩት የካምፓሱ ፕላንና ዳታ ማኔጅመንት ኃላፊ መ/ር መብራቱ ክፍሌ በበኩላቸው ስልጠናው በተመራቂ ተማሪዎች አዕምሮ ውስጥ ስለ ስራ ፈጠራም ሆነ የቅጥር ስራ ማፈላለግ ተነሳሽነትና ዝግጁነትን ለመፍጠር የስራው አለም ነባራዊ ሁኔታ ምን እንደሚመስልና ምን ዓይነት ክህሎቶች እንደሚያስፈልጉ ግንዛቤ ማስጨበጥ ላይ እንደሚያተኩት ጠቁመዋል።
በሀ/ዩ /የሙያ ማበልጸጊያ ማዕከል አስተባባሪና አሰልጣኝ መ/ር ከብረት ፍቃዱ ስልጠናው ከሁለት የትምህርት ክፍሎች ለተወጣጡ የ2017 ዓም ተመራቂ ተማሪዎች እንደሚሰጥና ከግንዛቤ ማስጨበጫነቱ ባሻገር በዓመቱ መጨረሻ ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር የማገናኘት እድልን የሚያካትት እንደሆነ ገልጸዋል።
