17/04/2018 ዓ/ም
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ “በኢትዮጵያ የአፍ መፍቻ ቋንቋን እንደ ማስተማሪያ ቋንቋነት መጠቀም” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ የፓሊሲ ዉይይት አካሂዷል።
የኮሌጅ ዲን ፕሮፌሰር ዘለቀ አርፍጮ የፖሊሲ ዉይይት መድረክ ሲዘጋጅ በኮሌጁ ታሪክ የመጀመሪያዉ መሆኑን ጠቅሰዉ በቀጣይም መሰል ዉይይቶች በተለያዩ ሀገራዊ እና ሳይንሳዊ ፋይዳ ባላቸዉ ጭብጦች ላይ በተከታታይነት እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡ የፖሊሲ ዉይይቱ አላማ ለፖሊሲ አዉጪዎች፣ አስፈጻሚዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በሳይንሳዊ ምርምር የተደገፈ ግብዓት መስጠት እንደሆነም ፕሮፌሰር ዘለቀ በመክፈቻ ንግግራቸዉ አስረድተዋል።
ለፓሊሲ ዉይይት የሚሆኑ ሀሳቦችን በማቅረብ እና ከተሳታፊዎች የቀረቡላቸዉን ጥያቄዎች በመመለስ የተሳተፉት ከጅማ ዩኒቨርሲቲ የተጋበዙት ዶ/ር ደመላሽ መንግስቱ እና ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተጋበዙት ዶ/ር ፈቀደ ምኑታ ሲሆኑ ዉይይቱን በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የፖሊሲ ልማት ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር መልሰዉ ደጀኔ መርተዉታል።

ህጻናት የመጀመሪያዎቹን የትምህርት አመታት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸዉ መማራቸዉ በራስ ቋንቋ የመጠቀም መብትን የሚያጎናጽፍ፣ ባህላዊ ማንነትን የሚያጠናክር፣ ህጻናት ትምህርትን በቀላሉ እንዲረዱ የሚያስቻል መሆኑን ጠቅሰዉ ይህም በአለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ህጎችና ፓሊሲዎች በግልጽ የተቀመጠና በስፋት እየተተገበረ ያለ ልምድ መሆኑንና በበርካታ ሳይንሳዊ ምርምሮች የተደገፈ መሆኑን ዶ/ር ደመላሽ መንግስቱ አብራርተዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ የአፍ መፍቻ ቋንቋን ለማስተማሪያነት መጠቀም በቂ እና የተጠና ዝግጅት ሳይደረግ ትግበራ ላይ ሲገባ በቂ እና የሰለጠነ የሰዉ ሃይል እና የትምህርት መርጃ ቁሳቁሶች ስለማይኖሩ እንዲሁም በርካታ ቋንቋዎችና ዘዬዎች ባሉበት አዉድ ዉስጥ ላልተጠበቀ አሉታዊ ዉጤቶች ሊዳርግ እንደሚችልና ይህም በእኛም አዉድ እንደተስተዋለ አጽንኦት ሰጥተዉ የተናገሩት ዶ/ር ፈቀደ ምኑታ ናቸዉ።
ሁለቱ ተመራማሪዎች ብዙም ባልተራራቀ ምክረ ሀሳቦቻቸዉ ህጻናትን በመጀመሪያዎቹ የትምህርት ክፍሎች ማስተማር ዉጤታማ እዲሆን ከተፈለገ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታን ከግምት ዉስጥ ባስገባ መልኩ ግልጽ የቋንቋ እና የትምህርት ፓሊሲ ማዉጣትን፣ የታቀደና የተቀናጀ የዝግጅት ሥራን፣ በቂ ሃብት መመደብንና ለጊዜያዊ ፖለቲካ አላማ ብቻ ሳይሆን ፍትሃዊ እና ዘላቂ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በንቃት በማሳተፍ መተግበር እንዳለበት ገልፀዋል።
በዉይይቱ ተገኝተዉ ማጠቃለያ ንግግር ያደረጉት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጥራት ማሻሻያ ዳይሬክተር ዶ/ር አቻምየለሽ ገ/ጻዲቅ መሰል የዉይይት መድረኮች መዘጋጀታቸዉ መምህራንና ተመራማሪዎች ያላቸዉን በሳይንሳዊ ጥናት የዳበረ ሀሳብ ለፖሊሲ አዉጪዎችና ሰፊዉ ማህበረሰብ እንዲያደርሱ ከማስቻሉም ባሻገር፣ ለትምህርት ጥራት መሻሻል አይነተኛ ሚና ስላለው ኮሌጁ ይህንን ማድረጉ የሚደነቅና ለሌሎችም ተሞክሮ የሚሆን ነዉ ብለዋል።
