Skip to Content

በሰላም ግንባታ ዙሪያ ከተማሪዎች ጋር የምክክር መድረክ ተካሄደ።

ታህሳስ 13/2018 ዓ/ም


ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ የሰላም ተቋም እና ላይፍ ኤንድ ፒስ ኢንስቲትዩት (LPI) ጋር በመተባበር ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስርዓት እና ከባቢ ለማስፈን በኮሌጆች መካከል ሊኖር ስለሚገባ አዎንታዊ ንግግር የውይይትና የምክክር መድረክ ታህሳስ 11/2018 ዓ.ም አካሂዷል።


የሀ/ዩ ፕሬዚደንት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አየለ አዳቶ በምክክር መድረኩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ዩኒቨርሲቲው ባለፉት አራት ዓመታት በሰላም ግንባታ ዙሪያ ተማሪዎች እርስ በርስ እንዲተዋወቁ እና አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የተቋሙ ማህበረሰብ በሰላም አስፈላጊነት ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲጨብጡ የሚያስችል ስራ መሰራቱን ገልጸዋል። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እና ከሌሎች ሀገራት ጭምር የመጡ በመሆኑ የተለያዩ ባህሎች፣ ታሪክ እና እሴቶች እንደሚኖራቸው የሚጠበቅ መሆኑን ጠቁመው ይህንን ማንነታቸውን የልዩነት ምክንያት ከማድረግ ይልቅ የአንድነት እና የመተባበር ኃይል አድርገው ሊጠቀሙ ይገባልም ብለዋል።

የዕለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር ወዳጄነህ መሀረነ በሰላም አስፈላጊነት ዙሪያ ከህይወት ተሞክሯቸው የተቀዳ ሰፊ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንደገለጹት አብዛኛዎቹ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡበት እድሜ ከአፍላነት ወደ ወጣትነት ሽግግር የሚደረግበት እድሜ እንደመሆኑ ለሚደርስባቸው የአቻ ግፊት ተጽዕኖ የሚሰጡት ምላሽ የተጠና ላይሆን እንደሚችል ገልጸዋል። ተማሪዎች ከተለያዩ ሱሶች እና አላስፈላጊ ተግባራት ራሳቸውን ጠብቀው የቤተሰብና የሀገር አደራ የተሸከሙበትን ዓላማ ከስኬት ለማድረስ ሰላምን በሚያመጡና በሚያስጠብቁ ድርጊቶች ላይ  መሳተፍ እንደሚገባቸዉ ዶ/ር ወዳጄነህ አሳስበዋል።


በመጨረሻም በዕለቱ በክብር እንግዳው በቀረበው መልዕክት ዙሪያ ከተማሪዎች በርካታ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች የተነሱ ሲሆን ምላሽ እና ማብራሪያም ተሰጥቶባቸዋል።

Share this post
Tags
Archive
ኮሌጁ በአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት ላይ የፓሊሲ ዉይይት አካሄደ።