Skip to Content

በአርቤጎና ወረዳ በኩታ-ገጠም የለማ የስንዴ ማሳ የባለድርሻ አካላት የመስክ ምልከታ ተካሄደ።

ታህሳስ 9/2018 ዓ/ም


በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ድጋፍ በሲዳማ ክልል አርቤጎና ወረዳ በጦ ቀበሌ በ17 አርሶ አደሮች ማሳ ላይ በኩታ-ገጠም የለማ የመኸር ስንዴ ማሳ ለመጎብኘት የአርሶ አደሮች የመስክ በዓል ታህሳስ 8/2018 ዓ/ም አካሂዷል::


በመስክ በዓሉ ላይ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችና ተመራማሪዎች፣ የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የግ/ተ/ሃ/ቢሮ፣ የማዕከላዊ ሲዳማ ዞን የግብርና መምሪያ፣ የአርቤጎና ወረዳና የበጦ ቀበሌ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም አርሶ አደሮች ተገኝተው ውይይት እና ግብረመልስ ተደርጓል።


የሀ/ዩ ፕሬዝደንት ዶ/ር ችሮታው አየለ በዚሁ ግዜ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ ጉድኝት ስራዎችን ለማሳደግ ለዘርፉ የሚደረገውን ትኩረት በማሻሻል አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ እየሰራ ነው። የመስክ ቀኑን ዓላማ ሲያስረዱም በጋራ የተሰራው ስራ ውጤት ማፍራቱን መመልከትና መገምገም እንዲሁም በቀጣይ ሊሰራ የሚገባው ስራ ላይ ለመመካከር መሆኑን ተናግረዋል።


የሀ/ዩ የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታፈሰ ማቴዎስ ጉብኝቱን ተከትሎ በተደረገው ውይይት ላይ ባስተላለፉት መልዕክት አዲሱን "ቦሩ" የተሰኘ የስንዴ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሮች በማቅረብ በአርቤጎና ወረዳ የታየውን ውጤታማ ሥራ ተከትሎ ዝርያውን በሌሎች አርሶአደሮች ማሳ ላይም ማስፋፋት ይገባል ብለዋል።


ዩኒቨርሲቲው ለወረዳው ያስተዋወቀው አዲሱን ለደጋ አከባቢ አየር ንብረት የሚስማማ እና ለዳቦ ምርት የሚሆነውን ቦሩ ስንዴ ብቻ ሳይሆን የአፈር አሲዳማነትን የሚቋቋም የገብስ ዝርያ፣ አኩሪ አተር እና የስንዴ ምርጥ ዘር ጭምር መሆኑን የገለጹት የክልሉ ግ/ተ/ሃ/ቢሮ  የግ/ገ/ፋ/አ/ግ/ ዳይሬክተር አቶ ሌጣ ለገሰ ሲሆኑ ከዩኒቨርሲቲዉ ጋር የግብርና ዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ በክልሉ እየተሰራ ያለው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸዉን እምነት ገልጸዋል።


የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ከሆኑ አርሶ አደሮች መካከል አቶ አስፋው አማሎ እና አቶ ሙላቱ ቱንሲሳ አሁን በአካባቢው ላይ ከፍተኛ የአየር ንብረት ለውጥ እየተከሰተና የስንዴ ምርታማነት እየቀነሰ ቢሆንም አዲሱ ቦሩ የስንዴ  ምርጥ ዘር ይሄንን ለውጥ ተቋቁሞ የተሻለ ምርት መስጠት እንደቻለ መስክረዋል::

Share this post
Tags
Archive
ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከሲዳማ ክልል ፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሃብት ልማት ቢሮ ጋር ሶፍትዌር ለማበልፀግ ውል ተፈራረመ።