ታህሳስ 7/2018 ዓ/ም
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ በስሩ ያለማውን የዕፅዋት ማዕከል አሁናዊ ሁኔታ ዳሰሳ፣ በዕፅዋት መድሃኒት ዙሪያ ያሳተመውን መፅሐፍ ለማስመረቅ እና ለማዕከሉ አስተባባሪና አጠቃላይ ሰራተኞች እውቅናና ምስጋና ለመስጠት ያሰናዳው መድረክ ዛሬ ተካሂዷል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር ችሮታው አየለ በመርሐግብሩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት የሰው ልጅ ህይወት ከእጽዋት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው መሆኑን ገልጸው ይኸውም ትስስር ለምግብነት፣ ለመድኃኒትነት፣ ለአካባቢ ጥበቃ እና ለገቢ ምንጭነት ከሚኖረው ጥቅም ባሻገር የሰውን ልጅ አስተሳሰብና ባህሪ በአዎንታዊ መልኩ ተጽዕኖ ማሳደር የሚችል የመንፈስ እርካታ በመስጠት እንደሚገለጽ ተናግረዋል። ዶ/ር ችሮታው አክለውም የእጽዋት ማዕከሉ (Botanical Garden) በኮሌጁ ብቻ ሳይሆን በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ስለእጽዋት እንክብካቤ ያለውን አመለካከት በሚታይ መልኩ እየቀየረ የሚገኝ መሆኑን ገልፀው በዚህ ስራ ውስጥ አሻራቸውን ላሳረፉ አካላት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።

የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ዙፋኑ በደዊ በበኩላቸው የእጽዋት ማዕከሉ ባለፉት አመታት በነበረው ጉዞ ከመማር ማስተማርና የምርምር ማዕከል ሆኖ ከማገልገል ባለፈ ከቱሪዝም አኳያ ከፍተኛኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ ሊያበረክት የሚችል መሆኑን ጠቁመው አሁን ለደረሰበት ስኬት የማዕከሉ አስተባባሪ ዶ/ር ፍሬው ከበደ እና ሰራተኞቹ ምስጋናና እውቅና መስጠት ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።
እጽዋት በባህሪያቸው የሰጠናቸውን እንክብካቤ ያክል ለእኛው መልሰው ጥቅም የሚሰጡ በመሆኑ፤ ሁሉም ሰው ሊጠብቃቸውና የራሱ አድርጎ ሊመለከታቸው እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ የእጽዋት ማዕከሉ ኃላፊ ዶ/ር ፍሬው ከበደ ናቸው።
በመድረኩ በኮሌጅ ደረጃ የተዘጋጀውና በእጽዋት ህክምና ዙሪያ የተጻፈው መጽሐፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
