ህሳስ 20/2018 ዓ/ም
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስር በሚገኙ የማስተማሪያ ግቢዎች (ካምፓሶች) መካከል በሀገር አቀፉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዓመታዊ የስፖርት ፌስቲቫል ላይ ዩኒቨርሲቲውን የሚወክሉ ብቁ ስፖርተኞችን ለመመልመል ታስቦ በ11 ዘርፎች ሲካሄድ የቆየው ስፖርታዊ ውድድር ታህሳስ 19/2018 ዓ.ም ተጠናቋል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር ችሮታው አየለ በማጠቃለያው መርሃ-ግብር ላይ ተገኝተው ሁሉም ተወዳዳሪዎች የውድድር ስሜትን ብሎም የእርስበርስ መግባባትን በመፍጠር ረገድ በውድድሩ ወቅት ላሳዩት መልካም ሥነ-ምግባር ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ስፖርት በእውቀትና በአካል ብቃት የተገነቡ ወጣቶችን ለማፍራት ትልቅ ሚና እንደሚጫወት የገለጹት ፕሬዚደንቱ ዩኒቨርሲቲውን በሀገር አቀፉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውድድር ላይ የሚወክሉ ተማሪዎች ውድድሩ ላይ ከመሳተፍ ባሻገር ውጤት በማስመዝገብና ባለፈዉ የዉድድር ዓመት የተገኘዉን ድል በዚህ ዓመትም በመድገም ዩኒቨርሲቲውን በመልካም ስም በማስተዋወቅ የአምባሳደርነት ድርሻቸውን እንዲወጡ አደራ ብለዋል።

በተ/ቀ/ሳ ኮሌጅ የስፖርት ሳይንስ ት/ክፍል ኃላፊ ዶ/ር ሲሳይ መንግሰቱ ለአንድ ሳምንት በዋናው ግቢ ስታዲየም ሲካሄድ የቆየው ውድድር በሰላምና በስኬት መጠናቀቁ እንዳስደሰታቸው ገልጸው ውድድሩ ብዙ ተተኪ ስፖርተኞች የተመለመሉበት መሆኑን ተናግረዋል።
የየውድድር ዘርፉ አሸናፊዎች የተለዩ ሲሆን፡-
በባህል ስፖርት እና በሴቶች አትሌትክስ አዋዳ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ፤
በቼዝ ውድድር ፣ በቴኳንዶ እና በወንዶች እግር ኳስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፤ በመረብ ኳስ በንሳ ዳዬ ግቢ፤ በቅርጫት ኳስ፣ በሴቶች እግር ኳስ፣ በጠረጴዛ ቴኒስ ፣ በወንዶች በአትሌቲክስና በአጠቃላይ በአትሌቲክስ ዋናው ግቢ በማሸነፍ የዓመቱ በዩኒቨርሲቲዉ ግቢዎች መካከል ሲካሄድ የቆየዉ ውድድር ሲያሸንፉ፤ የወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ የጸባይ ዋንጫ ተሸላሚ ሆኖ አጠናቋል።
በማጠቃለያ ፕሮግራሙ የተለያዩ የስፖርት ዘርፍ አሸናፊዎች የዋንጫ ሽልማት ሥነ-ስርዓት የተካሄደ ሲሆን ዩኒቨርሲቲውን የሚወክሉ ተጫዋቾች እና ተወዳዳሪዎች በጥር ወር አጋማሽ ጅማ ዩኒቨርሲቲ በሚደረገው ሀገር አቀፍ ውድድር ላይ እንደሚተፉ ይጠበቃል።
