ሕዳር 22/2018 ዓም
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ጥናት ማዕከል (CERVAS) ከኖርዌይ ኢምባሲ በተገኘ ድጋፍ (NORAD ICP-V ፕሮጀክት) በሲዳማ ክልል ሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ ሳማ ኤጀርሳ ቀበሌ በሚተገብረው የሐይቅ ዳር መሬት አጠቃቀም ሰርቶ ማሳያ ፕሮጀክት ላይ 10 ለሚሆኑ ስራ አጥ ወጣቶች፣ ሴቶችና ሞዴል አርሶ አደሮች የአንድ ቀን ተግባር-ተኮር ስልጠና ሰጥቷል።
የማዕከሉ ዳይሬክተርና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር ጌታቸው ስሜ ስልጠናውን በሰጡበት ወቅት ደለል አላስፈላጊ አረሞችን በማብዛት በሐይቁ ውስጥና በዙሪያው የሚገኙ የእጽዋትና እንስሳት ሀብቶችን ለአደጋ ተጋላጭ ስለሚያደርግ የአካባቢው ማህበረሰብ ከሐይቁ ሊያገኝ የሚገባውን ጠቀሜታ በብዙ እንደሚቀንስ ተናግረዋል።

ዶ/ር ጌታቸው እንዳሉት በፕሮጀክቱ ለአንድ ዓመት ያህል የተቀናጀ የሃይቅ ዳር መሬትና ተፋሰስ አጠቃቀም ለዘላቂ ስነምህዳር ግንባታና አገልግሎት ሰርቶ ማሳያ በዶሬ ባፋኖ ወረዳ በሳማ ኤጄርሳ ቀበሌ እየተሰራ ቆይቷል። ማዕከሉ ከወረዳዉ ግብርና ጽ/ቤት ጋር በመተባበር በዓሳ ኩሬ አዘገጃጀት (tilapia farming)፣ የተፈጥሮ ዓሳ መኖ አመራረት፣ አዘገጃጀት እና አመጋገብ (azolla farming and fish feeding)፣ የተቀናጀ የአትክልትና ፍራፍሬ አመራረት ዘዴ (regenerative agriculture-based horticultural production) እና የስኳር ድንች አመራረት እና የዘር ስርጭት ላይ ያተኮረ የመስክ ላይ ስልጠና ለስራ-አጥ ወጣቶች፣ እማወራዎች፣ ሞዴል አርሶአደሮች እና አካል ጉዳተኞች ተሰጥቷል።
የስልጠናዉ ዋና ግብ ተፈጥሮን መሰረት ያደረገ (Regenerative Agriculture) የዓሳ እና የዓሳ መኖ እርሻ መንደር እና የቋሚ ተክሎች እርሻ መንደር በመመስረት ለአካባቢዉ ማህበረሰብ የስራ ዕድል በመፍጠር፣ የምግብ እና የገቢ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ እንዲሁም የሃይቁንና ተፋሰሱን ስነምህዳር ማደስና መጠበቅ መሆኑ ተገልጿል።
