ታህሳስ 12/2018 ዓ/ም
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ የጂኦግራፊ መረጃ ሥርዓት ት/ክፍል በአለምአቀፍ ደረጃ በየጊዜው በዘርፉ የመጡ ለውጦችና አዳዲስ አሰራሮችን አስመልክቶ ግንዛቤ ለመፍጠር የሚከበረውን የ GIS ቀን ታህሳስ 10/2018 ዓም "Building Geospatial Skills for Ethiopia's Future" በሚል መሪ ቃል ያከበረ ሲሆን በዕለቱ ከአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን የትብብር መግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል።

የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ተሻለ ወ/አማኑኤል የGIS ትምህርት በዕለት-ተዕለት ህይወታችንም ሆነ በአጠቃላይ የአንድን አካባቢ መልከአምድራዊ ወሰንና ይዞታ ዘመናዊ በሆነ መልኩ በመመዝገብ ረገድ ከፍተኛ ሚና ያለው ዘርፍ መሆኑን ገልጸው በየጊዜው የሚመጡ አዳዲስ አሰራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን ከመጠቀም አኳያም በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል።
በኮሌጁ የGIS ት/ክፍል ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ሀብታሙ ታደሰ በዓሉ ላይ የትምህርት ክፍሉ ተማሪዎች እና ከአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የመጡ እንግዶችን ጨምሮ የኢትዮጵያ GIS ማህበር ፕሬዚደንት እና አባላት በበይነ መረብ ታድመው ፍሬያማ ውይይት አድርገናል ብለዋል።
በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ጉድኝት እና ዩኒቨርሲቲ-ኢንዱስትሪ ትስስር ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሶዶ በበኩላቸው የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት በዩኒቨርሲቲዎቹ መካከል ትውውቅ ለመፍጠር፣ አቅምን በማቀናጀት ለመተባበር እና ወደፊት በሚሰሩ የምርምር ስራዎች ላይ በማቀናጀት ሀገራዊ ፋይዳ ያለውን ውጤት ለማስመዝገብ የሚያስችል ነው ብለዋል።
